የእለቱ ጥቅስ

«በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም» ማርቆስ 9፡29

Site Last Updated:-Friday 3 September 2010
፩ የጥናትና ምርምር ማዕከሉ መመሥረት
ጥናትና ምርምር በሳይንሳዊ ዘዴ ለችግር መፍትሔ ለማፈላለግ፣ አዳዲስ ግኝቶችን ለመፍጠር፣ ተጨማሪ ዕውቀትን ለማግኘት፣ አስፈላጊውን መረጃ ይዞ ተገቢውን ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ ዛሬ አንቱ የተባሉ፣ ዓለምን  ያስደመሙ ጥበባት ኹሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ናቸው፡፡ በዘመናችን በዓለም ላይ የተጋረጡ በርካታ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ አካባቢያዊ፣ ፖለቲካዊና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ዋነኛው መንገድ ጥናትና ምርምር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በሀገራችንም ይህንን የሚያስፈጽሙ አያሌ ተቋማት ተመሥርተዋል፡፡ የሥልጣኔ ምንጭ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ለሆነችው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጥናትና ምርምር ሥራ ታላቅ ፋይዳ ያለው መኾኑ አያጠራጥርም፡፡ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የታሪክ ባላንጣዎች፣ የቅርስ ዘራፊዎች፣ የበዙበት ነው፡፡ በዚህ ዘመን እውነቱን ከሐሰት፣ ስንዴውን ከእንክርዳድ፣ በጉን ከተኩላ፣ ማሩን ከእሬት በመለየት ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሳይዛነፍ፣ ሳይቀየጥ፣ በክብር ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ የጥናትና ምርምር ሥራ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያላትን እምቅ ሀብት በአግባቡ ጠብቆ ለመያዝና ተጠቃሚም ለመሆን ለቤተክርስቲያን ውሳጣዊና ውጫዊ ችግሮች መፍትሔ ለመሻት፣ ቤተክርስቲያኗን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል የጥናትና ምርምር ሥራ ቸል ሊባል አይገባውም፡፡ በአጠቃላይ ጥናትና ምርምር የጎደለውን ለመሙላት፣ የተበተነውን ለመሰብሰብ፣ የተጎዳውን ለመጠገን፣ የጠፋውን ለመፈለግ፣ የተቀበረውን ለማውጣት፣ ዓይነተኛ መንገድ በመሆኑ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ወቅታዊ ጉዳይ ነው፡፡


ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያን ልጆችን በማስተባበርና ሁኔታዎችን በማመቻቸት በዕውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እናት ቤተክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ በማድረግ ላይ ያለ ማኅበር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንንም መንፈሳዊ ተግባሩን ለማከናወን በርካታ የአገልግሎት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም አንዱ የጥናትና ምርምር ማዕከል ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ማዕከል በተቋም ደረጃ ለማቋቋም የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የመመሥረቻ ሰነድ አዘጋጅቶ፡-


-    በ1996 ዓ.ም ከተወሰኑ የማዕከሉ አባላትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት እንዲካሄድበት አደረገ፡፡
-    በ1998 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጸሕፍት ጥናትና ምርምር ተቋም” በሚል ስያሜ ተቋቋመ፡፡ ተቋሙን በማስተዋወቅ ቀድሞ "መረጃና መዛግብት ክፍል" ሥር የነበረውን አነስተኛ ቤተመጻሕፍት በሥሩ እንዲሆን በማድረግ ቤተመጻሕፍቱን የማጠናከር ሥራዎችን ሠርቷል፡፡
-    በ1998 ዓ.ም. መጨረሻ  አጠቃላይ የመዋቅር ማስተካከያ ተደርጐ ተጠሪነቱ ለማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሓፊ ሆኖ ተግባርና ሓላፊነቱን በማስፋት "በማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጥናትና ምርምር ማዕከል" በመባል እንደገና ተደራጀ፡፡
-    በ1999 ዓ.ም. ማኅበሩ በነበረበት የሰው ኃይልና ሌሎች ችግሮች ምክንያት የታሰበውን ያህል ለመንቀሳቀስ አልቻለም ነበር፡፡
-    በ2000 ዓ.ም ለዕሥራ ምዕት በዓል አከባበር ዐቢይ ኮሚቴ ለነበረው የዐውደ ጥናትና ውይይት መርሐግብር ዝግጅት ክፍል ትኩረት ተሰጥቶ በመቆየቱ በመጠነኛ እንቅስቃሴዎች ብቻ ተገድቦ ቆይቷል፡፡ ነሐሴ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. የጥናትና ምርምር ልምድ ያላቸው ምሁራንና የቤተክርስቲያን አበው በተገኙበት ስለጥናትና ምርምር የተደረገው ውይይት የማዕከሉን ሥራ በማጠናከር ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
-    በወቅቱም ማዕከሉ መጠነኛ የስያሜ ማስተካከያ ተደርጎለት "የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል" ተብሎ የተሠየመ ሲሆን የማዕከሉን እንቅስቃሴዎች ለማማከርና ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ አሥራ አንድ አባላት ያሉት አማካሪ ቦርድ ተቋቁሞለታል፡፡ የማዕከሉ ዕቅድ በሥራ አመራር ጉባኤው ጸድቆለት ከኅዳር ወር 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡


፪  ዓላማዎች


የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል የሚከተሉት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት፡፡


-    ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ፣
-    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቅርሶች ላይ ጥናትና ምርምር በማካሔድ የቤተክርስቲያኗን መልካም ገጽታ በሚገነባ መልኩ ሥራ ላይ ማዋል፣
-    በጥናትና ምርምር የተገኙ ግኝቶችን ለሊቃውንቱና ምእመናን ማድረስ፣
-    የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች በማዘጋጀት በተመራማሪዎች እንዲጠኑ ማድረግ፣
-    የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የያዘና ደረጃውን የጠበቀ መደበኛ ዓመታዊ መጽሔት /journal/ ማሳተም፣
-    በቤተክርስቲያን ዙርያ ጥናት ለሚያደርጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሐሳብ፣ የሙያና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣
-    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ቀኖና፣ ትውፊትና ዶግማዋን፣ የጠበቁ መጻሕፍትን ማሳወቅ፣
-    ቤተመጻሕፍት፣ ቤተመዛግብትና ቋሚ ኤግዚብሽን (ሙዝየም) ማቋቀም፣ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል፣
-    በልዩ ልዩ ቦታዎች (በአገር ውስጥና  በውጭ) የሚገኙ መጻሕፍትንና መዛግብትን ማሰባሰብ፣
-    በቤተክርስቲያን ዙርያ የተጻፉ መጻሕፍት፣ የተጠኑ ጥናቶችና ቋሚ ቅርሶች ጠቋሚ /Directory/ ማዘጋጀት፡፡

፫  ዐበይት ክፍሎች


የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተደራጅቶ አገልግሎቱን እያበረከተ ይገኛል፡፡ ክፍሎቹም፡


-    የጥናትና ምርምር ክፍል
-    የቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ክፍል
-    የኅትመት፣ መርሐግብር ዝግጅት እና ገቢ አሰባሳቢ ክፍል ናቸው፡፡


ሀ. የጥናትና ምርምር ክፍል

ይህ ክፍል የሚከተሉትን ዐበይት ተግባራት ያከናውናል፡፡
-    በተለያዩ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ጥናትና  ምርምር እንዲካሔድ  ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር
-    ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ለአጥኚዎች መስጠት
-    ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ አጥኚዎችን ማዘጋጀት
-    በጥናትና ምርምር የሚያግዙ ሥልጠናዎችን መስጠት
-    በቤተክርስቲያን  የተጠኑ ጥናቶችን ማሰባሰብ
-    ለተመራማሪዎች የምክር አገልግሎት መስጠትና ሥራቸውን መከታከል
-    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጥናቶቻቸውን በቤተክርስቲያን ዙሪያ እንዲያካሂዱ ማበረታታትና ድጋፍ መስጠት
-    ለኅትመት የሚበቁ  የምርምር ሥራዎችን ማዘጋጀት
-    በጥናት ውጤቶች ቤተክርስቲያንን ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል
-    ወርኃዊ የሥነ ቤተክርስቲያን የውይይት መድረክ ማዘጋጀት
-    ዓመታዊ ዐውደጥናቶችን ማዘጋጀት
-    የጥናትና ምርምር መረጃ ቋት /Data Base/ ማዘጋጀት

ለ. የቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ክፍል

ይህ ክፍል የሚከተሉት መሠረታዊ ዓላማዎች ይኖሩታል፡፡

-    ቤተመጻሕፍትን፣ ቤተመዛግብትንና ቋሚ ኤግዚብሽንን (ሙዚየም) ማቋቋም፣ ማደራጀት
-    ለምእመናንና ለተመራማሪዎች የቤተመጻሕፍት፣ የቤተመዛግብትና የቋሚ ኤግዚብሽን አገልግሎት መስጠት
-    በልዩ ልዩ ቦታዎች (በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ) የሚገኙ መጸሕፍትንና መዛግብትን ማሰባሰብ
-    በአገር ውስጥም ሆነ  በውጭ አገር ከሚገኙ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ጋር ግንኙነት መፍጠር
-    በቤተክርሰቲያን ዙርያ በተጻፉ መጻሕፍት፣ መዛግብትና ቋሚ ቅርሶች ጠቋሚ /Directory/ ማዘጋጀት

ሐ. የኅትመት መርሐግብር ዝግጅት እና ገቢ አሰባሳቢ ክፍል

ይህ ክፍል የሚከተሉት መሠረታዊ ዓላማዎች ይኖሩታል፡፡
-    የምርምር ውጤቶችን በማሳተም  ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ማድረግ
-    የተለያዩ መርሐግብሮችን በማዘጋጀት የምርምር ውጤቶች በተመራማሪዎች እንዲቀርቡ ማድረግ
-    ማዕከሉን በልዩ ልዩ መንገዶች ከሌሎች መሰል እና ተባባሪ ተቋማት ጋር በማገናኘት ድጋፍ ለማግኘት ማስቻል
-    የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍና በማዘጋጀት ለማዕከሉ ገንዘብ ከተለያዩ ምንጮች ማፈላለግ
-    ለተመራማሪዎች ማበረታቻ የሚሆኑ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን ማድረግ

 

፬ የጥናትና ምርምር ማዕከል መልእክት


የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል አስቀድሞ የተገለጹትን ዓላማዎች አንግቦ እንቅስቃሴውን በስፋት ጀምሯል፡፡ ሆኖም ግን ማዕከሉ የተቋቋመለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ከተፈለገ የበርካታ ባለሙያዎች ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ሊኖር የግድ ነው፡፡ ስለሆነም የቤተክርስቲያን ልጆች፡-


-    የምርምር ጽሑፍ በማቅረብ (ጥናትና ምርምር በማካሄድ)
-    ለጥናትና ምርምር የሚያግዙ፣ ለቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት የሚሆኑ መጻሕፍትን፣ መዛግብትን፣ መረጃዎችን እና ቅርሶችን በማሰባሰብ
-    የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግ እና
-    ማዕከሉን በማንኛውም ነገር ሊደግፉና ሊተባበሩ ከሚችሉ ድርጅቶች ጋር በማገናኘትና በማስተዋወቅ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ መንፈሳዊ ግብዣችንን እናቀርባለን፡፡  
 
አድራሻ፦            በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
                               የጥናትና ምርምር ማዕከል
መ.ሳ.ቁ. 80078
አ.አ.
ኢትዮጵያ
ኢ-ሜይል፦  This e-mail address is being protected from spam bots, you need JavaScript enabled to view it

 
Difficulty with characters ?
Click here! if you have difficulty reading amharic(geez) characters
ያግኙን
አስተያየት፤ ጥያቄ ወይም ጥቆማ ካለዎት እዚህ ይጫኑ።
ምን ተለወጠ ?