|
በስመ አብ፣ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ።
የተወደዳችሁ ምእመናን፤
ልጆቻችሁ ከመዝሙር ጋር ደግሞ ሃይማኖታቸውን ፣ ስነምግባራቸውን እንዲማሩ ያስፈልጋል። ወደ ቤተክርስቲያንም ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ። ብቻችሁን ከመጣችሁ የምትሰሩትን አያውቁም፣ ወዴት እንደሄዳችሁ አያውቁም። ወራሹቻችሁ አይሆኑም። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ። አሳዩዋቸው። ስዕሉን ይሳሙ፤ ቅዳሴ ጠበል ይጠጡ። በእምነቱ አሻሹዋቸው፤ መስቀል እንዲስሙ አስተምሯቸው። ዕጣኑን ያሽትቱ፤ የሚታጠነውን፣ ስጋውን ደሙን ይቀበሉ ፤ ቃጭሉን ይስሙ፤ ደወሉ ሲደወል ይስሙ፤ ቄሳቸው ማን እንደሆነ፤ ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሆነች በውስጧም ምን ምን እንደሚሰራ ያጥኑ፤ ይማሩ። ወደ ሰንበቴም ስትሄዱ ይዛችኋቸው ግቡ ወደሰንበቴው፤ ዳቦዉን ተሸክመው ይምጡ፤ ይማሩ። እነርሱም ነገ ይህን እንዲወርሱ የነገ ባለአደራዎች መሆናቸውን እንዲያውቁ።
እንዲያው ዝም ብለን ብቻ ትምህርት ሲባል ሌላ ነገር እየመሰለን ነው እንጂ ትምህርቱን እናቶቻችን፤ አባቶቻችን አስቀምጠውልናል። ያንን መውረስ ነው ያቃተን እንጂ እነርሱ አዘጋጅተው አስቀምጠውልናል። ማህበሩ፣ ዝክሩ፣ ሰንበቴው፣ በቅዱሳን ስም በበዓል መሰብሰቡ፣ ማስቀደሱ፣ መቁረቡ፣ ቅዳሴ ጠበል መጠጣቱ ፣ መስቀል መሳለሙ ይህን ሁሉ አስቀምጠውልናል። ሌላ ምንም አዲስ ትምህርት አያስፈልግም ነበር። መመካት አይገባም እንጂ ፤ የሚገባ ቢሆን እኛ ከዓለም ሁሉ የበለጠ መመካት ይገባን ነበር። ምክንያቱም አባቶቻችንና አናቶቻችን ስርዓታችንን፣ እምነታችንን ሁሉ ሰፍረው ቆጥረው ያስረከቡን ስለሆነ ነው። እና ይህ ትውልድ ይህንን እንዳያጣ ነው አደራ የምንለው ። ይህ ትዉልድ ይህንን ከቀበረ በኋላ፤ ይህንን ካጠፋ በኋላ እንደገና ወደ ቤተ መዘክር እንዳይሄድ ነው። ሃይማኖቱን ፍለጋ፤ ታሪኩን ፍለጋ።
ስለዚህ እምነታችሁን ፣ ስርአታችሁንና መንፈሳዊ ዉርሳችሁን እንድትጠብቁ አደራዬ የጠበቀ ነው።
እግዚአሔር በበረከት ያትረፍርፋችሁ
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳጽ (1932-1982) ሚያዚያ 23 ቀን 1982 ዓ.ም በሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ለምእመናን ከሰጡት ትምህርት የተወሰደ
|