የእለቱ ጥቅስ

እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን - ራዕ. 2.10

Site Last Updated:-Friday 3 September 2010
የአሰቦት ገዳምን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ የልማት ፕሮጀክት ተጠናቆ ርክክብ ተካሔደ

በይበረሁ ይጥና

በምሥራቅ ኢትዮጵያ ምዕራብ ሐረርጌ ሃገረ ስብከት የሚገኘው የደብረ ወገግ አሰቦት ቅድስት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ገዳምን ችግር ለመፍታት በገቢ ራሱን እንዲችል የሚያግዝ የከብት ማድለብ ፕሮጀክት ሥራ ተጠናቆ ርክክብ ተደረገ፡፡

 

ገዳሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ፈርጀ ብዙ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቅ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ    የተለያዩ ችግሮች ደርሰውበታል፡፡ በተለይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግራኝ ወረራ፣ በፋሺስት ጣሊያን ወረራና በ1960ዎቹ መጨረሻ በሶማሊያ ጦርነት መነኮሳት አባቶች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡ ለከፍተኛ እንግልትና ሞትም ተዳርገዋል፡፡ እንደዚሁም በርካታ ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል ተቃጥለዋልም፡፡


ከየካቲት 26 እስከ መጋቢት 20 ቀን 2000 ዓ.ም በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ከአሥራ አንድ ሺሕ በላይ ሔክታር መሬት የሚሸፍን ጥንታዊ የደን ሀብት ወድሟል፡፡ የዚህ ደን መቃጠል ደግሞ ጉዳቱ ለገዳማውያኑ ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዝሀ ሕይወት ሀብት ልትከብርበት የምትችልበት በተለይም ለቱሪዝም ግብዓት ሊሆን የሚችል ነበር፡፡


ሌላው በገዳሙ ያሉ መናንያን የሚገለገሉበት የእርሻ መሬት በጣም ውስን ከመሆኑም ባሻገር በአካባቢው ተደጋጋሚ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት የሚመረተው ምርት በቂ ባለመሆኑ የገዳማውያኑን ሕይወት የሚፈታተን ሆኗል፡፡ እንዲሁም  በገዳሙ የንጹሕ ውኃ መጠጥ ከፍተኛ ችግር አለ፡፡


የገዳሙ አቀማመጥ በዙሪያው ካለው ሜዳማ መሬት ከፍ ብሎ ብቻውን እንደ ተራራ የሚታይ በመሆኑ የምንጭም ሆነ የወንዝ ውኃ በፍጹም ለማግኘት አይታሰብም፡፡ መናንያኑ ሕይወታቸውን የሚያቆዩት በክረምት ወራት የዝናብ ውኃ በማጠራቀም ከዚያች እየተቆነነች በምትሰጣቸው የመጠጥ ውኃ ነው፡፡
እነዚህን ተደራራቢ ችግሮች በማጤን የገዳሙን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ስለሚቻልበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ከገዳማውያኑ ጋር መከረ፡፡


በዚህም መሠረት በገዳሙ አቅራቢያ በአሰቦት ከተማ ዘመናዊ የከብት ማድለብ ፕሮጀክት ቢከፈት የገዳሙን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ያስችላል ከሚል ስምምነት ላይ ተደርሶ ፕሮጀክቱ ተነደፈ፡፡
ይህን አስመልክቶ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ አቶ ዘርዓየሁ ስሜ በሰጡት መግለጫ፤ «ፕሮጀክቱ ተነድፎ ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ተከናውነዋል፡፡ ሥራውን እውን ለማድርግ ከጎናችን የነበሩት ገዳማውያኑ፣ የመኢሶ ወረዳ አስተዳደርና የአርብቶ አደር ቢሮ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ተባባሪ ማኅበራትና የማኅበረ ቅዱሳን ቅርንጫፍ ማእከላት አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በገዳሙ የደን ቃጠሎ በደረሰ ጊዜም ከማጥፋት ጀምሮ በገዳሙ ውስጥ የነበሩትን  አላስፈላጊ ዕፅዋት ለማስወገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡


ዘመናዊ የከብት ማድለብ ፕሮጀክት ሥራ ሥንሠራ በዋናነት የከብቶች ቤት፣ የመኖ መጋዘን፣ ሲታመሙ ተለይተው የሚቆዩበት የከብቶች ማደሪያ ቤቶች ተሠርተዋል፡፡ በተጨማሪም የውኃ የመጠጫ ገንዳና የፍሳሽ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ተሠርቶ እንዳለቀ የሚደልቡት ከብቶች ግዥ ተፈጽሟል» ብለዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ሥራ ሂደት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ አቶ ዘርዓየሁ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የውኃና የዕቃ ማጓጓዣ ትራንስፖርት እጥረት፣ የሚፈለጉ የግንባታ ቁሳቁሶች በቅርበት አለመኖር፣ የዋጋ መናርና ለግንባታ ሥራ የሚውለው መሬት ተስማሚ አለመሆን ከችግሮቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ችግሮች እንደ መፍትሔ የተወሰዱት በማኅበረ ቅዱሳን የአሰበ ተፈሪ ማእከልና ዋናው ማዕከል በጋራ ሆኖ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበርና ተጨማሪ በጀት  በመመደብ ተግባራዊ መሆኑን አቶ ዘርዓየሁ ስሜ ጠቁመዋል፡፡


ጥር 8 ቀን 2002 ዓ.ም በአሰቦት ከተማ የከብት ማድለብ ፕሮጀክቱ ርክክብ ሲፈጸም የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ባሰሙት ንግግር፤ «የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ገዳሙ ቀጣይነት ያለው የመተዳደሪያ ገቢ እንዲኖርው ማድረግ ነው፡፡ ገዳሙ በልማት ራሱን እንዲችል ማድረግ ሁለት ጠቀሜታ አለው፡፡ የመጀሪያው ገዳማውያኑ ከቁሪትነት ጥንት ወደነበረበት አንድነት ገዳም እንዲሸጋገር ያግዘዋል፡፡ እስካሁንም መናንያኑ ካለባቸው ችግር የተነሣ ፕሮጀክቱ ሥራው ተጠናቆ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ለአንድ ዓመት በየወሩ ስምንት ሺሕ ብር በመመደብ በድምሩ በዓመት ዘጠና ስድስት ሺሕ ብር ማኅበሩ ደጉሟል፡፡


ሁለተኛው የዚህ ፕሮጀክት ጠቀሜታው በሀገረ ስብከቱም ሆነ በአጎራባች ለሚገኙ አህጉረ ስብከት የትምህርትና የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማእከል እንዲሆን ያስችለዋል» ሲሉ ተናረግዋል፡፡
ዘመናዊ ከብት ማድለብ ፕሮጀክትና ውኃ ለማስገባት በድምሩ ከሁለት መቶ አራት ሺሕ ስምንት መቶ ብር በላይ ወጭ ማድረጉን ዋና ጸሐፊው አመልክተው፤ ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ተባባሪ የሆኑትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡ በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን የአሰበ ተፈሪ የመኢሶ ወረዳ ማእከል፣ ናዝሬት፣ ጂጂጋ፣ ድሬደዋና ሐረር ማእከላት፣ እንዲሁም በእነዚሁ ከተሞች ለሚገኙ መንፈሳዊ ማኅበራት ምስጋና አቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚገኙ መንፈሳዊ ማኅበራትና ምእመናን፣ በሰሜን አሜሪካ ቺካጎ እና አፔነሲ ደብረ ዕንቁ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ብሎም በአውሮ¬ፓ ለሚገኙ ምእመናን ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል፤ ብለዋል፡፡


እንዲሁም የመኢሶ ወረዳ አስተዳደርና የአሰቦት ከተማ ከንቲባ ትብብር እንዳልተለየ አቶ ዳንኤል አመልክተው፤ ገዳሙ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኝ ብቸኛና ጥንታዊ በመሆኑ ከመንፈሳዊ ዕሴትም ባሻገር ለሀገር ለወገን ቅርስ፣ መኩሪያና ለቱሪዝም መስሕብ ስለሆነ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡


የመኢሶ ወረዳ አስተዳደርና ጸጥታ ሓላፊ አቶ ደበበ ሚኮ በበኩላቸው አስተዳደሩን ወክለው ባደረጉት ንግግር፤ «የእኛ ትልቁ ጠላት ድህነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ ፕሮጀክት ሀገራችን እየተከተለች ካለችው የልማት አቅጣጫ አንድ አካል ነውና የተሠራው ሥራ እጅግ በጣም አስደስቶኛል፡፡ ይህ የከብት ማድለብ ፕሮጀክት በዚህ ወረዳ የመጀመሪያው ለአካባቢው ሕዝብ አርአያነት ያለውና አስተማሪ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ተሞክሮ የሚገኝበት ብቻ ሳይሆን ለሰዎችም ሥራ ፈጥሯል» ሲሉ አወድሰው «በቀጣይም ተስፋፍቶ መቀጠል አለበት፡፡ በተለይም በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን እየተከተለች ካለችው እስትራቴጂ ሦስቱ ዲሞክራሲ ልማትና ሰላም አኳያ ሲታይ ይህን ልማት ማየት የሚያረካ ነው፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ክርስቲያኑና ሙስሊሙ ተቻችለው በመረዳዳት ማልማታቸው ለአካባቢው የሃይማኖት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ትልቅ አስተማሪ ነው፡፡ በቀጣይም አጠናክረው መቀጠል አለባቸው» ብለዋል፡፡


በርግጥም አቶ ደበበ ሚኮ እንዳሉት፤  ጥር 8 ቀን 2002 ዓ.ም የርክክቡ በዓል ዕለት ለማየት እንደተቻለው የበዓሉ ታዳሚዎች የክርስቲያኑና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በጋራ ነበሩ፡፡ በዚሁ ዕለት በአሰቦት ከተማ የሚገኙ አባቶችና እናቶች ትብብር የሚማርክ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ሙስሊም እናቶች «ሥራው የክርስቲያን ብቻ ነው» ሳይሉ ከሙስሊሙ ለተጋበዙ እንግዶች የሚሆን ምግብ ለማዘጋጀት ደፋቀና ሲሉ ተስተውለዋል፡፡


በገዳሙ ደን ቃጠሎ ጊዜም የከተማውን ከንቲባ ጨምሮ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እሳቱን ለማጥፋት በገዳሙ መገኘታቸውን በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በተለይ ከንቲባው ቃጠሎውን በምሽት ሲሰሙ በከተማው አባቶችን ደወል አስደውለው ሕዝቡን በማሰባሰብ መሣሪያቸውን ታጥቀው በቀዳሚነት መገኘታቸው ምን ያህል ለገዳሙ ትኩረት    መስጠታቸውን  የሚያመለክት ነው ተብሏል፡፡


ከንቲባው አቶ አብዱላኪም ዑስማንም ያረጋገጡልን ይህንኑ ነበር፡፡ «ገዳሙ በወረዳችን ብቸኛና የቱሪዝም ምንጭ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ነው፡፡ ይህም ለገዳሙ ድጋፍ የሚውል የከብት ማድለብ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን በጣም ጥሩና የሚበረታታ ነው፡፡ ወረዳውም አርብቶ አደር በመሆኑ ለድህነት ቅነሳው አርአያነቱ የጐላ ነው፡፡ በቀጣይ ማድለብ ብቻ ሳይሆን በከተማው የገበያ ትስስርም እንዲኖር እናስተዋውቃለን፡፡ ገዳሙ ከብት ለማድለብ እንደተነሳሳ ሁሉ የቱሪዝም ማረፊያ ቦታ ያስፈልገዋል፡፡ ስለሆነም ለምእመናንና ለቱሪስቶች ማረፊያ ሆቴል መሥሪያ ቦታ በዋናው መንገድ አጠገብ ለገዳሙ እንሰጣለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዳሙ ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ይህ ከሆነ የጎብኝዎች ቁጥር ይበዛል፤ ከተማዋም እየሰፋች የገበያ ትስስር እንዲኖር ያደርጋል» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡


ሌላው ፕሮጀክቱ ተነድፎ በተግባር ላይ እስኪውል ድረስ በቅርብ ሆኖ ምክርና ሙያዊ እገዛ በማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ያደረገው ሙስሊም ወጣት አቶ ዑመር መሐመድ ነው፡፡ አቶ ዑመር በመኢሶ ወረዳ የአርብቶ አደር ቢሮ የርቢና የድለባ ኤክስፐርት ባለሙያ ነው፡፡ አቶ ዑመር መሥሪያ ቤቱን በመወከልም ሆነ በግሉ ባደረገው አስተዋጽኦ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል፡፡ እኛም ትኩረታችንን ስለ ሳበው አነጋግረነው ነበር ፡፡


«ለዚህ ፕሮጀክት ገና ከጅምሩ አንሥቶ የምክርና ሙያዊም እገዛ ስናድርግ ቆይተናል፡፡ የምረቃው ቀን ደርሶ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ኪሳራ እንዳይደርስበት ምን ዓይነት ከብቶች መደለብ እንዳለባቸው፣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊደልቡ እንደሚችሉ፣ ብሎም እንዴት መደለብ እንዳለባቸው የሙያና የምክር አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ ከዚህ አንፃር የሠራነው ሥራ ፍሬያማ ሆኖ መታየቱ የሚያስደስት ነው» ካለ በኋላ ወጣት ዑመር፤ «በቀጣይ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በልማት ሥራ ላይ ቢሳተፉ ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት አረንቋ ትላቀቃለች፡፡» ሲል አሳስቧል፡፡


ምንም እንኳን የደብረ ወገግ አሰቦት ገዳምን ችግር በዘላቂነት ለመታደግ ጥረት ቢደረግም አሁንም ከግጦሽ ቦታዎች ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግር እንዳለ ተወስቷል፡፡ እንደዚሁም ባልታወቁ ግለሰቦች ከደኑ ውስጥ ዛፎች እየተቆረጡ እንደሚወሰዱ የተጠቆመ ሲሆን ይህን በሚመለከት ደግሞ የኦሮምያና የሱማሌ አጐራባች ክልል የጋራ ልማት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ንጋቱ ደምሴ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡


«እኛ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ከገዳሙ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ በተለይ ችግር በሚደርስበት ጊዜ ምግብ በመርዳት ጭምር ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ የሱማሌና የኦሮምያ አጉራባች ክልል የጋራ ጽ/ቤት አቋቁመን በጋራ እየሠራን ነው፡፡ አርብቶ አደሮች ከግጦሽ ቦታዎች ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ወደ ገዳሙ እንደሚገቡ እናውቃለን፡፡ ከዚህ በፊትም አስገብተው ራሳችን ሄደን ያስለቀቅንበት ወቅት አለ፤ አሁንም በገዳሙ የሚያስጠጉ ካሉ የግጦሽ ቦታውን ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ቃለ እገባለሁ፡፡» ካሉ በኋላ ስለ ፕሮጀክቱ ያላቸውን አስተያየት ሲገልጹ፤ «ይህ ፕሮጀክት በጣም ከጠበኩት በላይ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በልማቱ ሥራ ላይ ተሠማርተው መልካም ውጤታቸውን ማየት የመንግሥት ፖሊሲን ከማስፈጸም አንፃር ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ በአካባቢው ላሉ ማኅበረሰብ አስተማሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አካባቢያችን በአብዛኛው አርብቶ አደር ቢሆንም ከብት የማደለብ ልማድ የለውም፡፡ እናም በፕሮጀክቱ ተግባራዊነት እናስተምርበታለን ብዬ አምናለሁ» ብለዋል፡፡


ማኅበረ ቅዱሳን ከሌሎች ማኅበራት ጋር በመቀናጀት የተተገበረው የከብት ማደለብ ፕሮጀክት ተመርቆ ሲከፈት አሥራ አንድ የደለቡ በሬዎች፣ የመጠጫ ገንዳዎችና የመኖ መጋዘን ተጐብኝተዋል፡፡
በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የመንግሥት አካላት፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ማእከላትና ግለሰቦች በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ብርሃናት ከሃሊ በቃሉ የምስክር ወረቀቱን ከሰጡ  በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ «ልጆቻችን ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያን እድገት ልማት አሳስቧቸው የከብት ማድለቢያ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ በማድረግ ለምረቃ በማብቃታቸው በራሴና በሀገረ ስብከቱ ስም የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ የተራዳችሁና በዓሉን ለማክበር ዝግጅት ያደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል» ብለዋል፡፡


የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ገዳም አበ ምኔት ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ገብረ ጻድቅ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ሲሠራ ለተራዱ ሁሉ ምስጋና አቅርበው፤ «ገዳሙ ብዙ ተአምርና ታሪክ ያለው በመሆኑ ምንጊዜም እንዳትረሱት አደራ እላለሁ» ሲሉ አሳስበዋል፡፡


የአሰቦት ገዳም በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኝ ጥንታዊና ብቸኛ ገዳም ሲሆን በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በመኢሶ ወረዳ ልዩ ስሙ አሰቦት በሚባል በረሃማ ሸለቆ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡ ገዳሙ ከአዲስ አበባ ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከአሰቦት ከተማ ደግሞ በስተምዕራብ በኩል አሥራ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጥቅጥቅ ባሉ የተፈጥሮ ደኖችና በተከበቡ ተራራዎች ውሰጥ ይገኛል፡፡ ገዳሙ የተመሠረተው በጻድቁ በአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ አማካኝነት ነው፡፡ እኚህ አባት ከአሥራ ሁለቱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ገዳሙ የእናቶችና አባቶች በዓት ያለው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት አርድዕቱንና ደጅ የሚጠኑትን ጨምሮ ሁለት መቶ የሚሆኑ ገዳማውያን ይገኙበታል፡፡

 

 
< Prev   Next >
Difficulty with characters ?
Click here! if you have difficulty reading amharic(geez) characters
ያግኙን
አስተያየት፤ ጥያቄ ወይም ጥቆማ ካለዎት እዚህ ይጫኑ።
ምን ተለወጠ ?